በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ዋሽንግተን ኦሪገንና አይዳሆ ሀገረ ስብከት
የትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ ክፍል
ዑቅ እንከ ርእስከ በእንተ አንብቦ ወዘልፈ ሀሉ ባቲ፤ ወእመሰ ዘንተ ገበርከ ርእሰከሂ ወዘሂ ይሰማዐከ።
/፩ጢሞ ፬፥፲፮/
ራዕይ
በሀገረ ስብከታችን በኦርቶዶክሳዊ የነገረ መለኮት ትምህርት የበለጸጉ፤ በሙያና የሕይወት ክሂሎት የጎለበቱና ዘመኑን የዋጁ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ብቃት ያላቸው በየደረጃው ለሚሰጠው ሐዋርያዊ አገልግሎት በትጋት የሚፋጠኑ ካህናት እና ዲያቆናት እንዲሁም በሃይማኖት ጽኑኣን የሆኑና በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የሚኖሩ ምእመናን በዝተው ማየት፡፡
ተልዕኮ
ውጤታማ የትምህርትና ሥልጠና ዘዴዎችን በመጠቀም እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በጥራት ተዘጋጅተው የመንፈስ የአእምሮ እና የአካል ዕድገትን የሚያጎናጽፉ መንፈሳዊ ትምህርቶችን፤ የሙያ እና የሕይወት ክሂሎት ትምህርቶችንና ሥልጠናዎችን ለሀገረ ስብከታችን አገልጋዮች እና ምእመናን እንዲቀርብ ማድረግ፡፡
ዕሴቶች
- ጽኑ ሃይማኖት (መንፈሳዊነት):- የርትዕት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሥርዓትና ትውፊትን በመጠበቅና በማስጠበቅ በጽናት እናገለግላለን፡፡
- ክርስቲያናዊ ፍቅር:- የአገልግሎታችን ሁሉ ግብ የምእመናን ድኅነት ሆኖ አገልግሎታችን ሁሉ በፍቅርና በትጋት እንፈጽማለን፡፡
- የትብብር አገልግሎት:- የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ጠብቀን ለበጎ ተግባር ከተሰማሩ አካላት ጋር በቅንትና በትብብር እናገለግላለን፡፡
- ሐዋርያዊነት:- ያላመኑትን ማሳመንና ማጥመቅ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መሆኑን በማመን የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት ላላመኑት ለማዳረስ እና አዳዲስ አማኒያንን ለማፍራት እንተጋለን::
- ሁለንተናዊ ብቃት:- ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት ስልት በመከተል የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በጥራት፣ በስፋት እና በዘመናዊ አቀራረብ ለሁሉም እንዲደርስ እንጥራለን፡፡
- መተካት:- የነገዋን ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተረክበው በትጋት የሚያገለግሉ ትጉሓን ኦርቶዶክሳዊያን ወጣቶችን ለክህነትና ለሌላው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እናዘጋጀለን::
- ተጽእኖ ፈጣሪነት:- ማኅበረሰባዊ አገልግሎት ከቤተ ክርስቲያን ተግባራት አንዱ መሆኑን በመረዳት በምንኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ በሰብአዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በንቃት በመሳተፍ የቤተ ክርስቲያንን በጎ ተጽእኖ ፈጣሪነት እናረጋግጣለን::
ባለ ድርሻ አካላት/አጋሮች
-
ጠቅላይ ቤተ ክህነት
-
የሀገረ ስብከታችን መምሪያዎች
-
የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት
-
ማኅበራት /ለምሳሌ ማኅበረ ቅዱሳን ፣ማኅበረ ካህናት፤ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት፤ ማኅበረ በዐለ ወልድ ወዘይመስልዎሙ
-
ሌሎች ሀገረ ስብከቶችና በስራቸው ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት
-
አኃት አብያተ ክርስቲያናት
-
የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ
-
የተመረጡ የነገረ መለኮት ኮሌጆች
የትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ ተግባርና ኃላፊነት በቃለ ዓዋዲና ሕገ ቤተ ክርስቲያን የተመለከቱትን መነሻ በማድረግና ቃለ ዓዋዲው በሚፈቅደው መሠረት (ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 43 ተራ ቁጥር 3 እና በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 51 ተራ ቁጥር 4)የውጭ ሀገር ሁኔታን በማገናዘብ የተዘጋጀ፦
- የአብነት ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግ
- በመካከለኛ ጊዜ ግብረ ዲቁና እና ቅስና ላይ በማተኮር ተተኪ ዲያቆናትና ቀሳውስትን ማፍራት
- ትምህርተ ሃይማኖት ማስተማር
- በተለይ ሕጻናትና ተተኪ ወጣቶችን ማስተማርና ማሰልጠን
- የተሟላ የእንግሊዝኛ አገልግሎት ማዘጋጀት (አዲሱን ትውልድ ለመጠበቅና አዳዲስ ምእመናን ለማፍራት)
- ሥርዓተ ትምህርት ማዘጋጀትና ሰፊ የትርጉም ሥራ መስራት
- ቤተ መጻሕፍት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እንዲስፋፋ ማበረታታት
- የሙያና የሕይወት ክሂሎት አቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መስጠት
- የካህናትን አቅም ተከታታይነት ባለው ትምህርተ ኖሎትና ምክር አገልግሎት ሥልጠና ማሳደግ
- በተለያየ የእድሜ ክልል መሪዎችን ማፍራት
- የምእመናን አቅም በክርስቲናዊ ጋብቻ፤ የልጆች አስተዳደግ፤ የአእምሮና የአካል ጤና አጠባበቅ ሥልጠና ማሳደግ
- የኪነ ጥበብ ሙያ ሥልጠናዎችን ማበረታታት
- የተማሪዎች መመዘኛ ማዘጋጀትና አረጋግጦ የምስክር ወረቀት መስጠት
- የማሰልጠኛ ተቋም፣ የጥናትና መረጃ ማዕከል ማቋቋምና ማስተዳደር